ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ  ሰነድ ተፈራረመ

የመግባቢያ ሰነዱ በከተማስተዳደሩ  የሚወጡ አዋጆችን፣ ደንብና መመሪያዎችን በማተም በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግን መሰረት ያደረገ ነው፡፡

ሚያዚያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ አዳራሽ በተካሄደው የፊርማ ስነ-ስርዓት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ እንዲሁም የድርጅቱና የቢሮው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ቢሮው በከተማው የሚወጡ አዋጆችን፤ህግና ደንብና መመሪያዎችን ለከተማው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ አማራጮች  ሲሰራ መቆየቱንና ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ ማድረስ ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ይነሱ እንደነበርና በህትመት ዘርፍ የካበተ ልምድ ካለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በጋራ በመስራት የህትመት ውጤቶቹን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ቅሬታዎቹን ማስቀረት እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህግ ማርቀቅ እና ስርጸት  ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ መብራቴ የህግ ተደራሽነት ላይ የሚነሱ  ቅሬታዎችን  ለመቅረፍ ቢሮው እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው ህጎች ተደራሽ ካልሆኑ መውጣታቸው ብቻ በራሱ ግብ አይሆንም፤ የህግ እና የፍትህ  መጓደልን ያመጣል፤ በመሆኑም በቀጣይ  ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በመተባበር ህጎች  በተመጣጣኝ ዋጋ ታትመው ይሰራጫሉ ብለዋል፡፡

የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ የሚወጡ እና በምክርቤት የሚጸድቁ በርካታ ህጎችን ለፌደራል ፍርድ ቤቶች፣ ለከተማ ፍርድቤቶች እንዲሁም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች እና ለመላው ህብረተሰብ ህጉን ተደራሽ ማድረግ ለቢሮው የተሰጠ ተልዕኮ መሆኑን የገለፁ ሲሆን  አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ህጎችን የማተም ልምድ ስላለው ተልዕኳችንን ያሳካል ብለዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት የከተማ አስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ ከድርጅቱ ጋር በጋራ ለመስራት እድሉን በመስጠቱ አመስግነው ድርጅቱ በመደበኛና ምስጢራዊ ህትመት ሥራዎቹ ለበርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በተወካዮች ምክር ቤት እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቀው የሚወጡትን አዋጆችና ደንቦችን አትሞ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራን እየሰራ እንደሆነና በተመሳሳይ ከከተማ አስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ ጋር በተደረገው ስምምነት  መሰረት ፍትህ ቢሮ በከተማ አስተዳደሩ የሚወጡ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

አክለውም የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።