ድርጅቱ ለማዕከሉ ቀደም ሲል ሲያደርግ የነበረውን የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2016ዓ.ም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አስተባባሪነት በተዘጋጀውና የመንግስት የልማት ድርጅቶች በተሳተፉበት የጉብኝትና የድጋፍ መርሃ ግብር የአትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሪት ያሲሚን ወሃብረቢ፣ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ እና የተለያዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሪት ያሲሚን ወሃብረቢ ማዕከሉ ላለፉት አስራ ሁለት አመታት ይህንን በጎ ሥራ በመስራት ራሱን በማሳደግ ከ7500 በላይ ለሆኑ ወገኖች መጠለያ በመሆኑ የሀሳቡን አመንጪ ክቡር ዶ/ር ብንያም በለጠን ጨምሮ ሁሉም የማዕከሉ አጋሮችን አመስግነዋል፡፡
ክብርት ያስሚን አክለውም ማዕከሉ ያቀዳቸው ሁሉ እንዲሰምሩ በበመኘት ለዓላማው መሳካት ከጎን መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው ማዕከሉን በመጎብኘታቸውና ማዕከሉ አቅሙን አሳድጎ ለበርካታ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ተደራሽ መሆኑን በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ድርጅቱ ቀደም ሲል ሲያደርግ የነበረውን የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ግንዛቤ መውሰዳቸውንና በቀጣይም የድርጅቱን ማኔጅመንትና ሰራተኞች በማስተባበር ድጋፍ ማድረጉ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡