የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አመራርና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሔዱ
ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው የችግኝ ተከላና የቦታ ርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተወካይና የመስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ የሮን ተካልኝ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ማኑፋክቸሪንግ ፖርትፎልዮ ዳይሬክተር አቶ ሉላይ ዮሃንስ፣ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ እስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፤ የድሬ ሰኮሩ ወረዳ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተፈራ ባዩ፣ የድርጅቱ የማኔጅመንት አባላት፣ ቡድን መሪዎችና የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሸገር ከተማ አስተዳደር በኮራ ጅዳ ክፍለ ከተማ ድሬ ሰኮሩ ወረዳ ልዩ ስሙ ድሬ ግድብ እየተባለ በሚጠራ ስፍራ ለ20 ተከታታይ ዓመታት ባከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ አካባቢው ቀደም ሲል ከነበረው የአፈር መሸርሸር ከመግታት ብሎም የተሻለና ያማረ ገፅታ እንዲኖረው ከማድረግ እንዲሁም በአካባቢው ያለውን የአየር ንብረት ከማስተካከል አንፃር የላቀ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከተሰማራበት የህትመትና ተዛማጅ ሥራዎች ጎን ለጎን ማህበረሰቡን በተለያዩ አግባቦች ለመደገፍ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራን በዕቅድ አካቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዘርፉ ከሚሰራቸው በርካታ ሥራዎች መካከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ይገኝበታል፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለፁት ከህትመት ሥራው ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ገልፀው የህትመት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በዋናነት የሚጠቀምበት ግብዓት ወረቀት ከደን ውጤት እንሚሰራ አስታውሰው በዚህ መሰል የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች መሳተፉ ልዩ ቦታ እንደሚሰጠው ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ለበርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በሚሸፍነው ድሬ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ያለማቋረጥ በየዓመቱ የድርጅቱን አመራርና ሰራተኞች በማስተባበር የችግኝ ተከላና እንክብካቤው እንደቀጠለ ጠቁመው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገር አቀፍ ደርጃ ለተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር በማጣጣም ሀገር በቀል የሆኑ ችግኞችን በመትከል አሁን ላይ የሚታይ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለው ለሃያ አመታት በቀጠለው ጥረት በመጣው ውጤት ድርጅቱ ደስተኛ መሆኑን ገልፀው ለማልማት የተረከበው ቦታ ሙሉ በሙሉ በደን የተሸፈነ በመሆኑ በዘንድሮው መርሃ ግብር በቀረው አነስተኛ ቦታ ላይ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ቦታውን ለሸገር ከተማ መስተዳድር ለማስረከብ የእለቱ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተወካይና የከተማ አስተዳረሩ የአካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ የሮን ተካልኝ በበኩላቸው የችግኝ ተከላና የቦታ ርክክብ ለማድርግ በስፍራው ለተገኙት ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው ተፈጥሮን መንከባከብና አካባቢን መጠበቅ የሁሉም ዜጎች ግዴታ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥና እርሱን ተከትሎ ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽንና የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አይነተኛ አማራጭ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ የሮን ተካልኝ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደርጃ የተጀመረው እንቅስቃሴ የደን ሽፋንን በመጨመር፣የአፈር ለምነትን በማሳደግና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ አክለውም አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የአረንጓዴ አሻራን በሚደግፍ ሁኔታ ከ20 ዓመት በፊት በጀመረ ሥራ ለአካባቢው ግርማ ሞገስን ያለበሰ ደን እንዲታይ በማድረጉ በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነው የአካባቢው ማህበረሰብና የወረዳው አስተዳደርም በድርጅቱ የተጀመረውን መልካም ስራ በማስቀጠል የተዋበችኛ ለኑሮ ምቹ የሆነች ሀገርን ለትውልድ በማቆየት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የማኑፋክቸሪንግ ፖርትፎልዮ ዳይሬክተር አቶ ሉላይ ዮሃንስ በበኩላቸው በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ያሉና የሀገርን ኢኮኖሚ በመደገፍ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ድርጅቶች እንዲህ ባለ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በመሳተፍ የተሻለ ውጤት ሲያስመዘግቡ ማየት ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ጠቁመው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የአረንጓዴ አሻራ እምብዛም ባልተለመደበት ከ20 ዓመታት በፊት ጀምሮ ችግኞችን በመትከል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንክብካቤ በማድረግ ለዚህ ውጤት በማብቃቱ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡
የድሬ ሰኮሩ ወረዳ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተፈራ ባዩ እንደገለፁት ብርሃንና ሰለም ማተሚያ ድርጅት ቀደም ብሎ በሰራው የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ አካባቢው ከነበረበት መራቆት ወደ ደንነት መቀየሩን ማስተዋላቸውን ምስክርነት ሰጥተው ድርጅቱ ለአካባቢው አየር ንብረት መስተካከል ላበረከተው አስተዋፅኦ አመስግነዋል፡፡