የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ተገመገመ

የድርጅቱን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ  ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል መሰብሰብያ አዳራሽ ተገመገመ፡፡ በግምገማው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር ዶ/ር ብሩክ ታዬ  እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኦፕሬሽን፣ የፋይናንስ፣ ኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ የፕሮጀክት፣የትራንስፎርሜሽን እና ማህበራዊና አካባቢያዊ ግዴታዎች አፈፃጸም እንዲሁም በአፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮችንና ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱና በመወሰድ ላይ የሚገኙ ተግባራት እና የቀጣይ የትኩረት እቅጣጫዎች በድርጅቱ የስትራቴጂክ ስራ አመራር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መኮንን አበራ በኩል ቀርቧል::

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ውስጥ የኦፕሬሽን፣ የፋይናንስ፣ የፕሮጀክት/ኢንቨስትመንት እና የኮርፖሬት ገቨርናንስ አፈፃፀሞች በተመለከተ ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ውስጥ የነበረውን አፈፃፀም ግምገማ ግብረ መልስ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የማኑፋክቸሪንግ ፖርትፎልዮ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ልሉይ ዮሃንስ በኩል በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በአዲሱ የመመዘኛ መስፈርት መሰረት ተገምግሞ ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

 

በቀረበው ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል እና የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር ዶ/ር ብሩክ ታዬ እንደተናገሩት ድርጅቱ የበጀት ዓመቱን እቅድ አፈፃፀም ማሳካት አድንቀው በቀጣይ አመት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አያይዘውም ድርጅቱ አሁን ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ በሌሎች የህትመት ስራዎች ላይ  መስራት የሚገባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ በርካታ መንግስታዊ እና  መንግስታዊ ያልሆኑ ደንበኞች ያሉት ቢሆንም በግል ዘርፍ የተሰማሩ ደንበኞች ላይ በትኩረት በመስራት የደንበኞቹን ቁጥር መጨመር እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈፃሚው አሳስበዋል፡፡

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ የታዩትን ክፍተቶች በማስተካከል በቀጣይ ዓመት የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የገለፁት ዶ/ር ብሩክ  የድርጅቱን ችግር ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ በሆልዲንጉ በኩል ማንኛውም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በድርጅቱ ጊዜያዊ የፋይናንስ ሪፖርት መሰረት በ2016 በጀት ዓመት ውስጥ ብር 738,153,000 የሚያወጣ ምርት ለማምረት አቅዶ አፈፃፀሙ ብር 799,905,000 የሚያወጣ ምርት ለማምረት በመቻሉ አፈጻጸሙ 108.37% ሲሆን፣ ከተጣራ ሽያጭ ብር 1,400,840,000 ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ክንውኑ ብር 1,444,500,000 ሲሆን አፈጻጸሙ 103.12% መሆኑን ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በ2016 በጀት ዓመት 451,378,000 ለማትረፍ ታቅዶ 513,903,000 በማትረፍ ወይም የዕቅዱን 113.85% በማትረፍ በጀት ዓመቱን በስኬት አጠናቋል፡፡