በድርጅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች ጥረት ብቻ አጥጋቢ ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል በየሥራ ክፍሉ ያሉ ኃላፊዎች የኮቪድ መመሪያ መተግበሩን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከስራው ጋር በተቀናጀ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
በድርጅቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በተመለከተ የተከናወኑ ተግባራትንና ወቅታዊ ሁኔታውን አስመልክቶ ከህዝብ ግንኙነትና ማህበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር ቆይታ ያደረጉት በድርጅቱ የሰራተኛ ጤና አጠባበቅ ቡድን መሪ እና የኮሮና መከላከል አብይ ኮሚቴ አባል ሲ/ር አበባዬ መርዕድ እንደገለፁት ከመንግስት እና ከጤና ጥበቃ በወረደው መመሪያ መሰረት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሚወጡ መመሪያዎችን በመተግበር እና ይህን ጉዳይ የሚከታተል (ግብረ ሀይል በማቋቋም) ሰራተኛው ደህንነቱና ጤንነቱ ተጠብቆና ከቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ነፃ ሆኖ መደበኛ ስራዎች እንዲከናወኑ የመከላከሉ ስራ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ቡድን መሪዋ ገለፃ በተለያየ መልኩ የሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ጨምሮ ቫይረሱን ለመከላከል የድርጅታችን ሠራተኞች ስራ ቦታ ንክኪ ለመቀነስ በሚቻለው ሁሉ ስራዎች በስልክና በኤሌክትሮኒክስ ልውውጥ እንዲደረግ መደረጉን፤ የደብዳቤዎች ዝውውርን ለመቀነስም ስካን እየተደረጉ ወደ ሚመለከታቸው ክፍል እንዲላኩ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ፤ በጥበቃ ዙሪያ ለሚሰሩት አባላት ሰራተኞችና ባለጉዳዮች በሚወጡበትና በሚገቡበት ጊዜ የሚደረግ ፍተሻ ከንክኪ የፀዳ እንዲሆን መፈተሻ መሳርያ ተገዝቶ ጽዳቱ ተጠብቆ ስራ ላይ እንዲውል መደረጉን እና በድርጅቱ ክሊኒክ ለህክምና የሚመጡ ሠራተኞችን ስክሪን በማድረግ የኮቪድ 19 ምልክት ካላቸው ወደ ሚመለከተው ጤና ተቋም እስከሚላኩ የጊዚያዊ የለይቶ ማቆያ ክፍል በጤና ሚኒስቴር በወረደው መመሪያና መስፈርት መሰረት ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የድርጅቱ የስራ ባህሪ አልፎ አልፎ በቅርርብ የሚሰራ እና የስራ ቅብብሎሽ እና ንክኪ ያለው በመሆኑ እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ በርካታ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ተጋላጭነቱ ከፍተኛ በመሆኑ አስቀድሞ ምርመራ በማድረግ በመከላከል ዙሪያ ከፍተኛ ስራ በመሰራቱ የኮቪድ አስከፊነቱን በመከላክል ውጤታማ መሆን ተችሏል ያሉት ሲ/ር አበባዬ ወረርሺኙ በሀገራችን ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 700 ሠራተኞች የኮቪድ ምርመራ አድርገው 98 ሠራተኞች ላይ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው እና ከእነዚህ ዉስጥ 87 ሠራተኞች ያገገሙ እንዲሁም 11 ሠራተኞች በህክምና ክትትል ላይ የሚገኙ ሲሆን በወረርሽኙ ምክንያት ሞት አለመመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
የድርጅቱ ሰራተኛ ጤና አጠባበቅ ቡድን መሪዋ ኮቪድን ከመከላከል አንጻር በመንግስት የሚወርዱ መመሪያዎችን ከማስፈጸም አንጻር ድርጅቱ ያከናወናቸው ተግባራት ሲያብራሩ በድርጅቱ ውስጥ ኮቪድ-19 ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኮሚቴ ( ግብረ-ሀይል) በዋና ስራ አስፈጻሚ አመራርነት በም/ዋ/ስራ/አስፈ/ድጋፍ ዘርፍ ሰብሳቢነት መቋቋሙን እንዲሁም ከየስራ ክፍሉ የተውጣጡ ሠራተኞች በንዑስ ኮሚቴ በማቋቋም፣ዕቅድ አንዲዘጋጅ በማድረግ፣አስፈላጊ በጀት በመመደብ፣ በጤና ጥበቃ እና በመንግስት የሚወርዱ መመሪያዎችን ለመተግበር የሚያስችል ስራዎች እንዲሰሩ አድርጓል ብለዋል፡፡ በተያያዘም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት፣ የኮቪድ መመሪያዎቹ መተግበራቸው ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ የሰርቪስ አጠቃቀም፣ የሰው ሀይል በእረፍት መቀነስ ፣ውሀ፣ሳሙና ሳኒታይዘር ማሟላት፤ የኮቪድ ምርመራ ማድረግ፣ የለይቶ ማቆያ ክፍል ማዘጋጀት፣ ለጤና ባለሙያዎች ሙሉ የመከላከያ አልባሳት በማሟላት የኮቪድ 19 መከላከሉ ላይ ድርጅቱ ከፍተኛ ርብርብ እና አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል፡፡
ሲ/ር አበባዬ እንዳሉት በመጀመሪያ ላይ ኮቪድ መከሰቱ ሠራተኞች በመፍራትና በመጨናነቅ የስነ-ልቦና ጫና መፈጠር ይህ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በድርጅቱ ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕና አስክትሏል ብለዋል፡፡ አክለውም የህክምና ወጪ መጨመር፣ታካሚዎች በህክምና ዕረፍት ሲወጡ እና ቤት ሲቆዩ በድርጅቱ ስራ ላይ የሰው ሀይል ዕጥረት ማጋጠም በዚህ ምክንያት በስራ ላይ ባሉ ሠራተኞች የስራ ጫና ማስከተል እና ቀደም ሲል በሰርቪስ መኪኖች የወረደውን መመሪያ በማስከበር ወቅት የመኪና ምልልስ ስለነበር የትራንስፖርት ወጪ የመሳሰሉት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልፀው ነገር ግን በድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች ቁርጠኝነት በምርታማነቱ ላይ የጎላ ተፅዕኖ አላስከተለም ብለዋል፡፡
ኮቪድ-19 አሁንም በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ስርጭቱ እየጨመረ በመሆኑ በቀጣይም በመከላከሉ ዙሪያ መንግስት እና ጤና ሚኒስትር በሚያወርደው መመሪያ መሰረት ተግባራዊ በማድረግ ይበልጥ አጠናክረን በመስራት ስርጭቱን መግታት የሚያስችል ስራ መስራት አለብን ያሉት ሲ/ር አበባዬ በጤና ባለሙያዎች ብቻ መከላከል አጥጋቢ ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል በየሥራ ክፍሉ ያሉ ኃላፊዎች የኮቪድ መመሪያ መተግበሩን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከስራው ጋር በተቀናጀ መልኩ ቢሰራ ሠራተኛም ጤነኛ እና አምራች ይሆናል ድርጅቱም አትራፊና ምርታማ ይሆናል ብለዋል፡፡ በተያያዘም የድርጅቱ ሠራተኞች ስለ ኮቪድ-19 መጨናነቅ መፍራት ሳይሆን መከላከሉ ላይ መጠንከር እንደሚገባና ማስክ በአግባቡ መጠቀም፣በተቻለ መጠን እርቀት መጠበቅ፣እጃቸውን በሳሙናና በውሀ መታጠብ የውሃ እጥረት ካጋጠመ ሳኒታይዘር መጠቀም እና ባልታጠበ እጃቸው አይን፣አፍንጫንና አፋን አለመንካት እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚታዩ መዘናጋቶችን በማስወገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅረበዋል፡፡