የድርጅቱ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክተር የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ባዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ የሜዳልያና ሰርተፍኬት ተሸላሚ ሆኑ፡፡
ሽልማቱ የድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች የጋራ ሥራ ውጤት እንደሆነና ሙስናን በመዋጋት ረገድ የተጀመሩትን ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልፀዋል፡፡
የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክብርት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት መርሃ ግብር ላይ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከተመረጡና ሽልማት ከተበረከተላቸው አምስት የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ በመሆን የደርጅቱ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክተር የሜዳልያና የምስክር ወረቀት ተሸልመዋል፡፡
“ትኩረት ለትውልድ ሥነ ምግባር” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዓል ላይ የተሸለሙት የደርጅቱ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክተር አቶ መለሰ በቀለ ለሽልማት ያበቃቸው ኮሚሺኑ በ2013 በነበረው አፈፃፀም ከተቋማት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎች መካከል የተሻለ አፈፃፀም ስላስመዘገቡ እንደሆነና ሙስናን ከመከላከልና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር ግንባር ቀደም ሚና ካላቸው ተቋማት መካከል ብርሃንና ሰላም ተጠቃሽ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በ2013ዓ.ም በሥነ ምግባር መከታታያ ክፍል የሀብት ምዝገባ ሥርዓትን እውን በማድረግ፤የስነ-ምግባር መመሪያ በማዘጋጀትና ተግባራዊ በማድረግ፤ ለድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች በስነምግባር ዙሪያ ስልጠና በመስጠት፤ለሙስናና ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ጥናቶችን እንዲጠኑ ማድረግ መቻሉ ለሽላማቱ እንዳበቃቸው ገልፀው ሽልማቱ መነቃቃትን ከመፍጠር አንፃር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
አክለውም ሽልማቱ የድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች የጋራ ሥራ ውጤት እንደሆነና ሙስናን በመዋጋት ረገድ የተጀመሩትን ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልፀዋል፡፡