የድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች ለ18ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለገዳዲ ወረዳ ልዪ ስሙ ድሬ ግድብ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡
ሐምሌ 25/ 2013ዓ.ም በተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንዲሁም የማኔጅመንት አባላት የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች እና ከየሥራ ክፍሉ የተውጣጡ በርካታ ሠራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡
ድርጅቱ ከ18 ዓመታት በፊት በአካባቢው የጀመረውን የችግኝ ተከላና እንክብካቤ መርሃ-ግብር ሃገራዊ ከሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር አጣጥሞ በማስኬድ እንደ ሀገር የተያዘው ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ውጥን ላይ ድርሻውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝና ይህንንም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ገልፀዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለፃ ማተሚያ ድርጅቱ በዋናነት የሚጠቀመው የወረቀት ምርት ምንጩ ዛፍ እንደመሆኑ መጠን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፈጥሮን የመጠበቅን የመንከባከብ ሥራን ማከናወን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመው በአካባቢው የተከናወነው የችግኝ ተከላ ወደ ደንነት እንደተቀየረና በ2012 ዓ.ም ከተተከሉል ችግኞች ሰማኒያ በመቶ ያህሉ መፅደቃቸውን ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ ችግኝ ከመትከሉ ጎን ለጎንም በቋሚነት እንክብካቤ የሚያደርጉ ሰራተኞች በመቅጠር ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል መፈጠሩን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በየሩብ ዓመቱ ከድርጅቱ ሰራተኞችን በመላክ ደንና ችግኞቹ ያሉበትን ደረጃ ግምገማ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በእቅድ አካቶ ከሚያከናውናቸው የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች አንዱ በሆነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ የአፈር መሸርሸርን ከመግታት እና ስነ-ምህዳሩን ከማስተካከል ባሻገር ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች ወደ ደንነት በመቀየር ለአካባቢው ልዩ የሆነ ተፈጥሮአዊ ውበትን እንዳላበሱት ማየት ተችሏል፡፡