የሁለቱ ድርጅቶች ሥራዎች ተመጋጋቢ እና የላቀ ትስስር የሚፈልጉ በመሆናቸው በቀጣዩ ውጤት ማስገኘት በሚችል ደረጃ አብሮ መስራት እንደሚጠበቅ ተገለፀ፡፡
ከኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አ.ማ የመጡ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር አመራሮች የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ያነጋገሩ ሲሆን ሁለቱ ድርጅቶች አብሮ የሚሰሩበትን እና የላቀ ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት ድርጅቶቹ ውጤታማ የሚሆኑበት መንገድ ማመቻቸት የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ የሁለቱም ድርጅቶች ሥራዎች ተመጋጋቢ እና የላቀ ትስስር የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣዩ ውጤት ማስገኘት በሚችል ደረጃ አብሮ መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የብርሃና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከውጪ የሚያስገባቸውን የወረቀት ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ቢቻል ለድርጅቱ ዘላቂ ጥቅም ያስገኛል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አ.ማ ጋር የተሻለ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የህትመት ስራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
የብርሃና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የመሰረታዊ ሠራተኞች ማህበር የላቀ ተሞክሮ እንዳለውና ውጤታማ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አ.ማ የሠራተኛ ማህበር አመራሮች፤ ለስራ የሚረዳቸውን የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚፈልጉ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሰራተኛ ማህበር ተሞክሮውን እንዲያጋራቸው ጠይቀዋል፡፡ ባደረጉት የጋራ ውይይት የተሻለ ልምድ እንደ ቀሰሙ እና ለማህበሩ ሥራ የሚያግዛቸውን ተጨማሪ እውቀት እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ሊቀ-መንበር አቶ ተስፋለም ኃይሉ በበኩላቸው በመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበራቱ መካከል የተደረገው የልምድ ልውውጥ የተሻለ ሥራን በመስራት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡