የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አመራርና ሰራተኞች ለ19ኛ ጊዜ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ

ድርጅቱ ሀገራዊ ፕሮግራሙን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ሁሉ ድርሻውን እንደሚወጣ ተጠቆመ፡፡ 

ሐምሌ 24/2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፊንፊኔ ዙሪያ ድሬ ግድብ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለን ጨምሮ የማኔጅመንት አባላትና ከየሥራ ክፍሉ የተውጣጡ ሰራተኞች ተሳትፈውበታል፡፡

ለ19ኛ ጊዜ በተካሄደውና የድርጅቱ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎቹ አንዱ የሆነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዓመት አንድ ጊዜ መጥቶ ከመትከል ባሻገር በቋሚነት ችግኞቹን የሚጠብቁና የሚንከባከቡ ሠራተኞችን በመቅጠር እንዲሁም በየሩብ ዓመቱ በቦታው በመገኘት ክትትል በማድረግ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

ያነጋገርናቸው የችግኝ ተከላው ተሳታፊዎች አንደገለፁት አካባቢውን ድርጅቱ እንዲያለማው ሲደረግ ምንም አይነት ዛፍ ያልነበረበትና በክረምት ወቅት የሚከሰተው ዝናብ ደለል ወደ ግድቡ ያስገባ እንደነበር አስታውሰው ይሁንና ዛሬ ላይ ቀደም ባሉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ወደ ደንነት በመቀየራቸው የአካባቢውን ገፅታ ውብ ከማድረጋቸውም በላይ ወደ ግድቡ የሚገባውን ደለል መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ በዋና የህትመት ግብዓትንት የሚጠቀመው ወረቀት ከመሆኑና ወረቀት ደግሞ የደን ውጤት ከመሆኑጋር ተያይዞ ለችግኝ ተከላና እንክብካቤ ትኩረት መስጠቱ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ የሚያምኑት የተከላው ተሳታፊዎች  በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ቀደም ብሎ የጀመረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንደገለፁት፤ ለህትመት አገልግሎት የሚውለው ወረቀት የደን ውጤት በመሆኑ ድርጅቱ ድሬ ግድብ አካባቢ ቦታ በመረከብ ባለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት ችግኝ ሲተክል መቆየቱንና ድርጅቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በማጠናከር ባለፉት አመታት የተተከሉት አብዛኞቹ ችግኞች መፅደቃቸውን አስረድተዋል። አያይዘውም ድርጅቱ በማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በብዙ መልኩ እየተሳተፈ እንደሆነ ገልፀው ሀገራዊ ፕሮግራሙን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ሁሉ ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡