የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ነባር የቦርድ ሥራ አመራር አባላት በክብር ተሸኙ

ሐምሌ 8/2011 ዓ.ም በግዮን ሆቴል በተዘጋጀው የሽኝት መርሃ-ግብር ድርጅቱን በቦርድ አመራርነት ሲያገለግሉ ለነበሩ አባላት የምስጋና እና እውቅና የመስጠት ሥራ ተሰርቷል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ለተሸኙ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የተዘጋጀውን ስጦታ እና ሠርተፊኬት ያበረከቱላቸው ሲሆን፤ ጠንክሮ ለሠራ ሰው የማበረታቻ ሽልማት መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ተሸኚ ነባሩ የቦርድ አባላት የተጣለባቸውን የሥራ ኃላፊነት ተቀብለው ድርጅቱን በቅንነት አገልግለዋልም ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሰው በተሰማራበት ሥራ መስክ ውጤታማ ተግባር መፈጸም ትልቁና እና ቁልፍ ጉዳይ ነውም ብለዋል አቶ ወርቁ፡፡

ከተሸኙ የቦርድ አመራር አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አማኑኤል በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በአጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ እና ትርፋማነቱን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እንዳጋጠሙት ጠቁመው፤ አሁን የተገኘውን ውጤታማነት ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ የበለጠ ትርፋማ እና ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በቀጣይነት ተባብሮ እና በአንድነት መስራት ይጠበቃል ብለዋል አቶ አማኑኤል፡፡ በመጨረሻም አቶ ወርቁ ለተሸኙ የቦርድ አመራሮች ባስተላለፉት መልዕክት መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል፡፡