የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በ2011 ዓ.ም. የደረጃ ሁለት ሰልጣኞችን ተቀብሎ ማሰልጠን ጀመረ፡፡

የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በ2011 ዓ.ም. የስልጠና መርሃ ግብሩን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በህትመትና ግራፊክስ አርት ኦፕሬሽን(Printing and graphics art operation)የደረጃ ሁለት ሰልጣኞችን ተቀብሎ ማሰልጠን መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ህትመት ቴክኖሎጂው የትምህርትና ስልጠና ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አስቻለው አብደላ እንዳሉት፤ ኮሌጁ የደረጃ ሁለት ሰልጣኞችን ተቀብሎ የማስተማር ሥራውን የጀመረው በህዳር ወር 2011 ዓ.ም. መሆኑን ጠቁመው የህትመት ቴክኖሎጂው የህትመት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችለውን የተለያዩ የትምህርት መስኮችን በደረጃና በአጫጭር ስልጠናዎች በመከፋፈል ቅድመ ዝግጅቶቹን በማጠናቀቅ ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡ አቶ አስቻለው አያይዘው ሰልጣኞቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኮሌጅ መግቢያ የሚሆን ነጥብ ያመጡ እና ቀደም ብሎ በኮሌጁ የደረጃ አንድ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው የመመዘኛ ነጥብ (COC) ወስደው ያለፉ ናቸው ብለዋል፡፡ በደረጃ ሁለት ትምህርታቸውን በማታና በቀን እየተከታሉ ያሉ ሰልጣኞች ከ40 በላይ ናቸው ያሉት አቶ አስቻለው ለስልጠና ማስጀመሪያ አስፈላጊ የሆኑትን ግብዓቶችን በተቻለ መልኩ ተሟልተው ነውም ብለዋል፡፡ በቀጣይ የስልጠና ጊዜያት መሰረታዊ የሆኑ እና የትምህርት ደረጃው የሚፈልገው ማሽኖችና ቁሳቁሶች እየተለዩ በግዥ እንደሚሟሉ ጠቁመዋል፡፡ የስልጠና አሰጣጡን ምቹ እና መማር የሚፈልጉ ሰዎችን ተደራሽ እንዲሆኑ ስልጠናው በቀንና በማታ መርሃ ግብር እየተሰጠ መሆኑም ታውቋል፡፡ ስልጠናው የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርትን አጣምሮ የያዘ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው የመመዘኛ ፈተና COC በመውሰድ በደረጃው አንደሚመረቁ ተጠቁሟል፡፡

በህትመት ኮሌጁ የደረጃ ሁለት ስ ልጠናቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን አድንቀው በቀጣይ በተሻለ መልኩ ተጠናክሮ እንዲሰጥና የተሻለ እውቀትና ክህሎት ገብይተው እንደሚመረቁ አስረድተዋል፡፡ ተማሪ ሚኪያስ ቴዎድሮስ የደረጃ አንድ ስልጠናውን አጠናቆ ለደረጃ ሁለት የሚያበቃውን መመዘኛ በመውሰድ በስልጠና ላይ ሲሆን የደረጃ ሁለት ትምህርት በንድፈ ሀሳብና በተግባር እየተሰጠ መሆኑን ጠቁሞ የመማር ማስተማር ሂደቱም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡ ሌላኛዋ የደረጃ ሁለት ተማሪ የሆነችው ሰብለወንጌል ጳውሎስ በበኩሏ የትምህርት አሰጣጡ በጥሩ ሁኔታ እየተሰጣቸው መሆኑን በመጠቆም በስልጠናው በቂ እውቀትና ክህሎት እንደሚቀስሙበት ገልጻለች፡፡ ኮሌጁ የተሟላ የማጣቀሻ እና አጋዥ መጽሐፍቶችን አደራጅቶ የያዘ በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሂደት የተሻለ እንዲሆን አድርጎታልም ተብሏል፡፡

በህትመት ኢንዱስትሪው ውስጥ በመግባትም በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ መስራት ያስችለናል ስትል ተማሪ ሰብለወንጌል ተናግራለች፡፡ የህትመት ኮሌጁ ስልጠና ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ አደረጃጀቶችን እና ለስልጠናው የሚውል አጋዥ መጽሐፍቶች ዝግጅት ሲያከናውን የቆዩ እና ለህትመቱ ዘርፍ አቅም የሚሆንና በዘርፉ የተማረ የሰው ሀይል በማፍራት በተሻለ ደረጃ ምርታማነትን የሚያሳድግ የህትመት ኮሌጅ መከፈቱን ያደነቁት አቶ አስቻለው የህትመት ኮሌጁ ወደ ሚፈለገው ደረጃ እንዲያድግ የቁሳቁስ እና ማሽን አቅርቦት እንዲሁም መምህራንን የማሟላትና የማብቃት ሥራ በቀጣይ የሚሰሩ የቤት ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡