የድርጅቱ የፐብሊሺንግና ኤዲቲንግ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ በድሉ ሴብሎስ በድርጅቱ የተቋቋመው የፐብሊሺንግ የሥራ ክፍል የተለያዩ ረቂቅ ጽሁፎችን ከደራሲያን ፣ ከአዘጋጆች ፣ከተርጓሚዎች ፣ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት በጨረታና በቀጥታ በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት ጽሁፎችን በሚመለከተው ሙያተኛ አስገምግሞና የአርትኦት ስራ አሰርቶ እንደሚያሳትም፣ ለሽያጩ እና ለማስተዋወቅ ስራ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያድርግ ገልፀው ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸውንና ሀገራዊ ትሩፋት በሚኖራቸው ርዕሰ ጉዳች ዙሪያ ሙያተኞችን በማሰባሰብ እንደሁኔታው በውስጥ አቅም ጥናት በማስጠናት የተለያዩ ጽሁፎችን አዘጋጅቶ በማሳተም ለድርጅቱ ትርፍ፣ ምርትና ሽያጭ ስራ አስተዋጽኦ እያደገ ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ በድሉ ድርጅቱ የፐብሊሺንግ ስራ በማከናወኑ ስለሚኖረው ተቋማዊና ሀገራዊ ፋይዳ ሲያብራሩ ድርጅቱ በፐብሊሺንግ ክፍል በኩል የሚያሳትማቸው መጻህፍት የማህበረሰቡን የመግዛት አቅም ግምት በማስገባት በአነስተኛ ዋጋ አብዛኛው ህብረተሰብ ክፍል መጻህፍት መግዛት እንዲችል ዕድል እንደሚፈጥር ብሎም አንባቢ ፣ ጠያቂ ፣ በሰከነና በበሰለ መንገድ መልስ መስጠት የሚችል ትውልድ እንዲፈጠር ፣ ወጣትና ጀማሪ ጸሀፊዎችን በማበረታታት ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ በማድረግ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት እንደሚያስችለው እና ለመጽሀፍ አዘጋጆች ፣ ደራሲያን ፣ለግምገማና አርትኦት ሙያተኞች የስራ እድል መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
ቡድን መሪው ረቂቅ ጽሁፍ ከመቀበል አሳትሞ ለገበያ እስከ ማቅረብ ያለውን ሂደት ሲያብራሩ የረቂቅ ጽሁፎች ፕሮፖዛል በጨረታና በቀጥታ ከተሰበሰቡ በኋላ (በጨረታ የቀረቡት በድርጅቱ የግዥ መመሪያ መሰረት የሚገመገሙ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ፕሮፖዛላቸው ማሟላት ያለበትን ዝርዝር የጽሁፉ ይዘት ፣ለህብረተሰቡ የሚኖረው ፋይዳ ፣ የደራሲው/የአዘጋጁ ግለ ታሪክ ፣ የክፍያ ሁኔታና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ያካተተ ከሆነ ከኤዲቶሪያል ኮሚቴ እና ከዋና ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ በኋላ ረቂቅ ጽሁፉን አቅርቦ በሙያተኞች እንዲገመገም ተደርጎ የግምገማ ሂደቱን ካለፈ ውል በመዋዋል የአርትኦትና የማናበብ ስራ ተሰርቶ በደንበኞች አገልግሎት ግምት ወጥቶለት እንደሚታተም እና መጻህፍቱ ተጠናቀው መጋዘን ከገቡ በኋላ በድርጅታችን የመሸጫ ሱቆችና በተላያዩ የመጻህፍት መደብሮች ለሽያጭ ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
አቶ በድሉ አያይዘውም በድርጀቱ በፐብሊሺንግ ክፍል የሚታተሙት መጻህፍት በሚመለከታቸውና ልምዱ ባላቸው ሙያተኞች የሚገመገሙና የአርትኦት ስራ የሚሰራላቸው በመሆናቸው የይዘት ችግር፣ በንባብ ጊዜ አንባቢን ከንባብ የሚያደናቅፉ ፊደላትና ሃሰቦች እንዳይኖሩ በከፍተኛ ጥንቃቄና ክትትል የሚሰሩ ናቸው ፡፡ የመጻህፍቱ መሸጫ ዋጋ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል መግዛት አቅም ከግምት ያስገባ በመሆኑ በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ያደርገናል፡፡
ለሽያጭ ያቀረብናቸውን መጻህፍት በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ያሉ አሳታሚዎች፣ የመጻህፍት መደብሮችና አከፋፋዮች የሚሰሩትን አሰራር በመከተል በጅምላ ለሚገዙ ደንበኞች 35% ቅናሽ ማድረግ በመጀመራችን በገበያ ውስጥ ዘልቀን ለመግባት ያስችለናል፡፡ ይህ ቅናሽ የማምረቻ ዋጋን ፣የአዘጋጆች/የደራሲያን፣ የገምጋሚና የአርታኢያን ክፍያን የማያካትትና የድርጅቱን ጥቅም የማይጎዳ ሲሆን የመጻህፍቱ መሸጫ ዋጋ ሲወሰንም የማምረቻ ወጪን ሳይነካ የቅናሹ መጠን ታስቦበት የሚወሰን በመሆኑ በድርጅቱ ላይ የሚያስከትለው ጫና አይኖርም ብለዋል ፡፡
የምርቶቹን የጥራት ደረጃ ከማስጠበቅ አኳያ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ለተነሳላቸው ጥያቄ የፐብሊሺንግ ስራ ውድድሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ሲሆን የመጻህፍቱ ይዘት ፣የመጻህፍቱ የህትመት፣ የጥራዝ እና የአስተሻሸግ ጥራት፤ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ እንዲሁም ለገበያ በቶሎ አትሞ ማቅረብና የመሸጫ ቦታዎች ዋናዋና የውድድሩ መለኪያዎች እንደሆኑ ጠቅሰው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከቅድመ ህትመት ጀምሮ እስከ ማጠናቀቅ ባለው የስራ ሂደት ውስጥ ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገው ድጋፍ፣ክትትልና ቁጥጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም የሚደረገውን ድጋፍ፣ክትትልና ቁጥጥር አጠናክሮ በመቀጠል የጥራቱን ደረጃ በማሳደግ ከሚመለከታቸው የስራ ክፍል ሀላፊዎችና ሙያተኞች ጋር በመመካከርና በቅንጅት መስራት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ቡድን መሪው የመጻህፍት ዝግጅት፣ግምገማና አርትኦት የመሳሰሉት ስራዎች በፐብሊሺንግ ክፍሉ ባሉ ሙያተኞች የሚሰራ ቢሆንም ረቂቅ ጽሁፉ በመጽሀፍ መልክ በጥራትና በሚፈለገው ጊዜ አትሞ ፣ለገበያ ማቅረብና በመሸጥ በኩል በርካታ ክፍሎችና ሰራተኞችን ጥምረት የሚፈልግ ስራ እንደመሆኑ ፤ ስለፐብሊሺንግ ስራ በድርጅታችን ውስጥ በየደረጃው የተሟላ ግንዛቤና የባለቤትነት ስሜት አለመፈጠሩ ለስራ ማነቆ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ መጻህፍቱን በሚፈለገው ጊዜ አትሞ ለገበያ አለማቅረብና ይደርሳል የሚል ቅን አመለካከት መኖሩ ነው፡፡ በተጨማሪም የፐብሊሺንግ መጻህፍት ሽያጭ ባህሪ እንደ መደበኛ ሌላ የህትመት ውጤት በአንድና በሁለት የተቋሙ ሱቆች ብቻ ሸጦ መጨረስ እንደሚቻል መታሰቡና ከዚሁ መንገድ ለመውጣት ግዜ መውሰዱ ይጠቀሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እነዳለ ሽያጩ የሚከናወንባቸውን የተለያዩ አማራጮችን ያለመጠቀምና በመጻህፍት ሽያጭ ስራ አለም አቀፍ የሆነውን የቅናሽ አሰራር ገፍቶ አለመሄድ የሚጠቀሱ ማነቆዎች መሆናቸውን ቡድን መሪው ጠቅሰው እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት ስለፐብሊሺንግ ስራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በሰፊው መስራት ፤ለህትመት የተላለፉት ስራዎች በጊዜው ለገበያ ባለመቅረባቸው ድርጅቱ የሚያጣውን ጥቅምና ገጽታ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእኖ በተጨባጭ እንዲያውቁት ማድረግ ፤ የመጻህፍትን ሽያጭ ሂደት ከሌሎች ዓለምአቀፍና የሀገር ውስጥ አሳታሚና አከፋፋዮችን ተሞክሮ በማየት ከሌሎች መጻህፍት መደብሮች ጋር በጋራ መስራት፤ እንዲሁም የተጀመረውን የውክልና ሽያጭ (ኮንሳይመንት) አሰራር አጠናክሮ መቀጠል ያሉብንን ማነቆዎች ሊቀርፉ የሚችሉ የተወሰኑ መፍትሔዎች ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
አቶ በድሉ በሀገራችን የፐብሊሺንግ ስራ በተለይም የመጽሀፍ ፐብለሺንግ በስፋት ያልተሰራበትና ለህብረተሰቡ ታማኝና ሃላፊነት፣ጥሩ ስም እንዲሁም ትልቅ አቅም ያለው ተቋም የሚፈልግ ስራ እንደሆነና ለዚህ ደግሞ ተመራጭ ከሚሆኑት በጣት ከሚቆጠሩ ተቋማት መካከል ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አንዱ እንደሆነ ገልፀው ስለዚህም ይህን መልካም እድል በአግባቡ በመጠቀም ወጤታማ ለመሆን ሁላችንም መተጋጋገዝና በጋራ መስራት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡