የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የማኔጅመንት አባላት፣ የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች እና ሰራተኞች ለሜቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ አደረጉ፡፡

“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!”  በሚል መርህ  በበጎ ፈቃደኛ ክቡር ዶ/ር ቢኒያም በለጠ ለአርባ  አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን ድጋፍ እንክብካቤ  በማድረግ  የተጀመረው ሜቄዶንያ  የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል፤ አረጋውያንንና የአዕምሮ ህሙማንን ዘር፣ ሃይማኖትና ፆታ ሳይለይ በተለያዩ የሥራ መስኮችና የኃላፊነት ደረጃዎች  ተሰማርተው ሀገራቸውንና ወገናቸውን  ሲያገለግሉ የነበሩ ነገር ግን ጉልበታቸው በደከመና ሰርተው ራሳቸውን ማስተዳደር በማይችሉበት ጊዜ ጧሪ አጥተው ጎዳና ላይ የወደቁ  አረጋውያንን እና በተለያዩ ቦታዎች ወድቀው የሚገኙ የአዕምሮ ህሙማንን በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት በማንሳትና ወደ ማዕከሉ በማምጣጥ የህክምና፣ የመጠለያና የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ በማደርረግ  አሁን ላይ ከሁለት ሺህ  በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን በቤተሰብነት በመያዝ እጅግ ሰብኣዊ በሆነ ተግባሩ ዓመታትን ተሻግሯል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በዕቅድ አካቶ ከሚያከናውናቸው በርካታ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በተጨማሪ የሜቄዶንያን በጎ ተግባር በአካል ተገኝቶ ለማየት እንዲቻል የጉብኝት መርሃ ግብሩን ያመቻቸ ሲሆን በጉብኝቱ የድርጅቱ ማኔጅምንት ፣ የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር አመራሮች እና ሰራኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ጉብኝቱ ቅዳሜ ታህሳስ 20 ቀን 2011ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን ከድርጅቱ ለማዕከሉ እንዲሰጥ የተወሰነው ብር 250,000 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) እና ከሰራተኞች የተሰበሰበ ብር 8,800 (ስምንት ሺህ ስምንት መቶ ብር) ቼክ አቶ ተካ አባዲ ለማዕከሉ መስራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ አስረክበዋል፡፡

በተያያዘም በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን ምሳ የማብላት መርሃ-ግብር የተከናወነ ሲሆን ጉብኝቱን የተካፈሉ የድርጅቱ አመራርና ሰራተኞች በሂደቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡