በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት የሠራተኞች ዓመታዊ በዓል በድምቅት ተከበረ

በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሰራተኞች በዓል መስከረም 25/2012 በድርጅቱ ቅጥር ግቢ በድምቀት የተከበረ ሲሆን የድርጅቱ የ2012 ዓ.ም መሪ ዕቅድ እና የ2011 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም አጭር ሪፖርት ቀርቧል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ሽታሁን ዋለ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የ2011 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም በተለይ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት የተለያዩ ችግሮች ያጋጠመ መሆኑን ገልጸው በድርጅቱ የቦርድ አመራር፣ በማኔጅመንቱ፣ በሠራተኛ ማህበርና በጠቅላላው ሠራተኞች ልዩ ትብብር ዕቅዱ እንዲሳካ ተደርጓል፡፡ አያይዘውም ለበጀት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም ተግዳሮት ናቸው ያሏቸውን ለበዓሉ ተሳታፊዎች የገለጹ ሲሆን የማተሚያ ማሽን ማርጀት፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር እና ሌሎች በዋናነት አንስተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የ2012 ዓ.ም ዕቅድ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ መሠረት እንዲሳካ የሁሉም ሠራተኞች ትብብርና አብሮ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ ሽታሁን፡፡ ከተሳታፊዎች የተነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን ተቀብሎ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡

የድርጀቱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ወርቁ ጓንጉል ለሠራተኛው የስራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት በድርጅቱ ያለው የማሽን እጥረት እና ያረጁ ማሽኖች በአዲስ መተካት እንዳለባቸው ጠቁመው ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ ቦርዱ እንደ ቦርድ እየሰራበት ይገኛል ብለዋል፡፡

በድርጅቱ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና በጡረታ ለተገለሉ ከ40 በላይ ለሚሆኑት የድርጅቱ ሠራተኞች ድርጅቱ እውቅና የመስጠት እና ምስጋና አቅርቧል፡፡ የሥራ ጊዜያቸውን አጠናቀው በጡረታ ለተሸኙ ሰራተኞችም ሥጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡