ድርጅቱ የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የተለያዩ የቅድመ መከላከል ሥርዓቶችን በመዘርጋት ሰራተኞችን ከበሽታው ለመታደግ እና ተልዕኮውን ለመወጣት ጥረት እያደገ መሆኑን አስታውቋል

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወርዱ መመሪያዎችን በማስፈፀም እና ሌሎች በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ አጠቃላይ የምርት ሥራዎች በጥንቃቄ እንዲተገበሩ በማደረግ እና የተለያዩ የቅድመ መከላከል ሥርዓቶችን በመዘርጋት ሰራተኞችን ከበሽው ለመታደግ እና ተልዕኮውን ለመወጣት ጥረት እያደገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በድርጅቱ ያለው የሥራ ሁኔታ ቀደም ሲል እንደነበረ ቢቀጥል ሰራተኞችን ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚያደርግ ስለነበረ ሁኔታዎችን በማጤን አፋጠኝ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ የድርጅቱን ሰራተኞች ከበሽታው ለመከላከል እንዲቻል ለሰራተኞቹ ስለ ወረርሽኙ ግንዛቤ በማስጨበጥ፤ ተጋላጭ የሆኑ ሰራተኞችና አሰራሮች ላይ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ በአጠቃላይ ድርጅቱ የቫይረሱን ሥርጭትን ለመግታት የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚያስተባብርና የሚከታተል ኮሚቴ ተመስርቶ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን በድርጅቱ የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ አንዳርጌ ገለፁ፡፡

እንደ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገለፃ መንግስት በቫይረሱ ዙሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና የህትመት ሚዲያዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ሁሉ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሰራተኞችም ከሚዲያና ከአካባቢያቸው ከሚያገኙት ግንዛቤዎች ባሻገር በድርጅቱ ሚኒ ሚዲያ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች እና ወቅታዊ መረጃዎችን በሚሰራጭበት የድርጅቱ ቴሌቪዥን የተለያዩ ትምህርትና መረጃ ሠጪ ቪዲዮዎች እየተላለፉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በተያያዘም በቫይረሱ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ የያዙ በራሪ ወረቀቶች፣ብሮሸሮች፣ ፖስተሮች ተዘጋጅተው በማሰራጨት ሰራተኛው ግንዛቤው እንዲያድግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ በዋናነት የሚተላለፈው በንኪኪ እንደመሆኑ መጠን ሰራተኞች የሚኖራቸውን ንክኪ እንዲቀንሱ ከማድረግ ባሻገር እጆቻቸውን እንዲታጠቡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ያሉት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ሰራተኞችም ሆነ ወደ ድርጅቱ የሚመጡ ደንበኞች ወደ መስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን የሚታጠቡበት የቧንቧ ውሃ እንዲሁም ሳሙና እንደተዘጋጀና ለሰራተኞች በነፍስ ወከፍ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እና የእጅ ማፅጃ (ሳኒታይዘር) እደላ እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡ ለድርጅቱ ለጤና ባለሙያዎች የተለያዩ የመከላከያ አልባሳት እንዲቀርብላቸው የተደረገ ሲሆን ሰራተኞች ዘወትር ጠዋት ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የሙቀት መጠናቸውን በመለካት ወቅታዊ የሰራተኞች የጤና ሁኔታ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ አያይዘው ገልፀዋል፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ድርጅቱ ስብሰባዎችን አለማድረግ፣ በምርት ክፍሎች ሰራተኞች ተራርቀው በመቀመጥ ሥራዎቻቸውን እንዲሰሩ ማድረግ፣የጤና እክል ያለባቸውን ሰራተኞች ከስራ ገበታ መለየት፣ የሰራተኞች ካፍቴሪያ አጠቃቀም ጥንቃቄን ያማከለ እንዲሆን ማድረግ፤የሥራ አካባቢዎችን በቂ እና ንፁህ አየር እንዲያገኙ ማድረግ፤የበሽታውን ምልክት ለሚያሳዩ የማቆያ ቦታ ዝግጅት እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚያደርጉ ሲሆን የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጁ ትምህርት እንዲቋረጥ መደረጉንና የዓመት ፈቃድ ያላቸው ሰራተኞች ሥራን በማይበድል መልኩ እረፍት እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል የኮሚቴው ሰብሳቢ፡፡

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ አካቶ የሚሰራቸው ሥራዎች የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን መከስት በድርጅቱ አፈፃፀም ላይ ተፅዕኖ ማስከተል የጀመረ ሲሆን በቀጣይም በምርት፣በሽያጭና ትርፍ ዕቅድ አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ይጠበቃል ያሉት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ የወረርሽኙን ሥርጭት መግታት እና ድርጅቱን ወደቀደመው እንቅስቃሴው የመመለስ ሥራ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስታውሰው ሁላችንም በቫይረሱ ላለመያዝ ከምናደርገው ጥንቃቄ ባሻገር ሌሎችን ግንዛቤው የሌላቸውን ዜጎች በማስተማር ሰብአዊ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡