የብርሃንና ሰላም ህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በህትመት ቴክኖሎጂና ግራፊክ አርት ሙያ ያሰለጠናቸውን 37 ተማሪዎች አስመረቀ

ድርጅቱ የህትመት ኮሌጁን ለማሳደግና በዘርፋ ለመሠልጠን ፍላጎት ላላቸው ዜጎች አይነተኛ አማራጭ በመሆን ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ሚያዚያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በግዮን ሆቴል በተካሄደው የምረቃ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሪት መልዕክት ሳህለን ጨምሮ   የድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣የድርጅቱ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች እና የማኔጀመንት አባላት፣የኮሌጁ መምህራንና ሰራተኞች፣ተመራቂ ተማሪዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ምረቃ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሪት መልዕክት ሳህለ ባደረጉት ንግግር ለድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ፣የማኔጅመንት አባላት፣የኮሌጁ መምህራንና ሰራተኞች፣በተለይ ለተመራቂ ተማሪዎች እና የተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ክብርት ወ/ሪት መልዕክት ሳህለ ድርጅቱ አንድ መቶ አመታትን ያስቆጠረ አንጋፋና ፈርቀዳጅ ከመሆኑም ባሻገር በዘርፉ የመሪነትን ሚና እየተጫመተ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን ገልፀው ከቴክኖሎጂ ሽግግርና የሰው ሃይል ስልጠና ላይ በትኩረት መስራቱ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ስር ካሉና መልካም አፈፃፀም ካላቸው ድርጅቶች መካከል ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አንዱ እንደሆነ የገለፁት ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ የህትመት ዘርፍን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመራ ከማድረግ ብሎም በቀጣይ በዘርፉ ከሚፈለገው የሠለጠነ የሰው ሀይል ከማቅረብ አንፃር በኮሌጁ የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በኢትዮጵያ በህትመት ዘርፍ ሙያ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግርን ለመቅረፍ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ከፍቶ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ በህትመት ዘርፍ ያካበተውን ልምድ በተደራጀ መልኩ ለዜጎች ለማስተላለፍ እንዲችል በከፈተው ኮሌጅ በርካቶች ሰልጥነው ወደ ሥራ መግባታቸውን መረዳት ተችሏል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ (ህትመት ዘርፍ)  አቶ ጌታሁን ነጋሽ እንደገለጹት ኮሌጁ  የተቋቋመው በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩትን ባለሙያዎች በማሰልጠን በህትመት ዘርፍ የሚታየው ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አብሮ የሚሄድና ቴክኖሎጂውን በአግባቡ ሊጠቀም የሚችል የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የድርጅቱን ምርታማነትና ትርፋማነት ለማሳደግ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ በህትመት ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ሃይል  እጥረት ለመቅረፍ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም በሀገር ደረጃ ለዘርፉ በተዘጋጀው የሙያ ደረጃ መሰረት ጥራት ያለውንና ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና መስጠት የሚያስችለውን የሥልጠና ወርክሾፖችና ግብዓት በማደራጀትና በማሟላት ሠልጣኞችን ተቀብሎ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው ኮሌጁ ለህትመት ድርጅቶችና ለዩኒቨርሲቲዎች በህትመት ዙሪያ የማማከርና የህትመት ማሽን ጥገና አገልግሎት በመስጠት ብሎም በተለያዩ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

ድርጅቱ የህትመት ኮሌጁን ከማሳደግና በዘርፋ ለመሠልጠን ፍላጎት ላላቸው ዜጎች አይነተኛ አማራጭ በመሆን ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በትኩረት እየሰራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ጌታሁን በህትመትና ግራፊክ አርት ሰልጥነው ለምረቃ ለበቁ ተመራቂ ተማሪዎች መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ካሳ ባስተላለፉት መልዕክት

ኮሌጁ በ2008 ከአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ በተሰጠው የማሰልጠን እውቅና መሰረት ከድርጅቱ ውጪ ለሚመጡ የስልጠና ፈላጊዎች የትምህርትና ሥልጠና ዕድል በመክፈትና የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን፤ እንዲሁም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሶስት ሥልጠና በመስጠት በዘርፉ የሚታየውን የሰጠለነ የሰው ኃይል ችግር ከመቅረፍ አኳያ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡  አክለውም ኮሌጁ ትኩረቱን በህትመት ዘርፍ ላይ ብቻ በማድረግ በ2010 ዓ.ም የማሰልጠን ፍቃድ ከፌደራል  ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ በማግኘት በሀገር ደረጃ ለዘርፉ በተዘጋጀው የሙያ ደረጃ መሰረት ጥራት ያለውንና ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና መስጠት የሚያስችለውን የሥልጠና ወርክሾፖችና ግብዓት በማደራጀትና በማሟላት በህትመትና ግራፊክ አርት ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሶስት እንዲሁም የአጫጭር ጊዜ ሥልጠናዎች በህትመት ቴክኖሎጂ፣ በግራፊክ ዲዛይንና አርት፣ በህትመት ዋጋ ትመና እና በሲልክ ስክሪን ህትመት ሠልጣኞች ተቀብሎ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የኮሌጁ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ካሳ በመልዕክታቸው ኮሌጁ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለውጪ ሰልጣኞች በአጭር ጊዜ ሥልጠና በግራፊክ ዲዛይንና አርት 1598፣ በህትመት ቴክኖሎጂ 184 ፣በህትመት ዋጋ ትመና 128 እና በሲልክ ስክሪን 18 ሰልጣኞችን በማሰልጠን የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ በተማሳሳይ በ2014 ዓ.ም በደረጃ ሶስት በተመሳሳይ ሙያ ያሰለጠናቸውን 31 ተማሪዎች ማስመረቁን እስታውሰው ለሁለተኛ ጊዜ በደረጃ ሶስት የህትመትና ግራፊክስ አርት ሙያ የተመረቁትን 37  ተማሪዎች የአንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ክብርት ወ/ሪት መልዕክት ሳህለ ለተመራቂዎች ዲፕሎማ በመስጠት መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡

በዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች ለአሰልጣኝ መምህራኖቻቸው የማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል፡፡