በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የቴምብር ህትመት በአዲስ መልክ መታተም ጀመረ

 በውጭ ሀገር እየታተሙ የነበሩ የህትመት ዓይነቶችን በሀገር ውስጥ ለማተምና እየወጣ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ቀደም ባለው ዘመን በድርጅቱ ሲታተሙ ከነበሩት በርካታ የመደበኛና የሚስጥራዊ የህትመት ውጤቶች አንዱ ቴምብር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሀገራችን ያለውን የቴምብር ህትመት ፍላጎት ሲያሟላ የነበረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በአንድ ወቅት የቴምብር ህትመት ሥራው ከእጁ መውጣቱ ይነገራል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ ረዘም ላሉ ዓመታት ህትመቱን አቋርጦት የነበረውን ቴምብር በአዲስ መልክ ማተም ጀምሯል፡፡ በድርጅቱ የምስጢራዊ ህትመት ዳይሬክተር ተወካይ የሆኑት አቶ በየነ ጀምበሬ እንደገለፁት ከውጭ የሚገባው ለቴምብር ህትመት የሚውለው ጥሬ ዕቃ እጥረት በማጋጠሙ ህትመቱ ተቋርጦ እንደነበርና በውጭ ሀገር ሲታተም መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ በሚስጢራዊ ህትመት ያካበተውን ከፍተኛ ልምድ በመጠቀም ወደ ውጪ እየተላኩ የሚታተሙትን የህትመት ውጤቶች በሀገር ውስጥ በማተም የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ ከመወጣት ባሻገር ለድርጅቱም ሆነ ለሀገር የሚኖረውን ዘረፈ ብዙ ጥቅም መነሻ በማድረግ  የቴምብር ህትመት ሥራ በአዲስ መልክ ለማስጀመር መታሰቡን አቶ በየነ ይገልፃሉ፡፡

የቴምብር ህትመት ሥራ  በድርጅቱ መሠራቱ የድርጅቱም ሆነ በሀገራችን ላሉ ቴምብር ለሚጠቀሙ ተቋማት ብሎም እንደ ሀገር የሚኖረው ፋይዳ በርካታ መሆኑን የሚገልፁት አቶ በየነ ደንበኞች በሚፈልጉት መጠንና ዓይነት ታትሞላቸው እጅግ ባጠረ ጊዜ መረከብ ከመቻላቸውም በላይ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ከመቀነስ አንፃር የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የቴምብር ህትመት ፍላጎት በመረዳት በድርጅቱ ለማተም ከአሳታሚው ተቋም ጋር ከተደረጉ ምክክሮች ጀምሮ ለህትመቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከማሟላት እና አትሞ እስከ ማስረከብ ያሉ በርካታ ሂደቶችን  በጥንቃቄና የድርጅቱ ምርትና ምርታማነት ላይ እሴት መጨመር በሚያስችል መልኩ መሰራቱንና የተገኘውም ውጤት ደንበኞችን ያስደሰተና ይበል የሚያሠኝ መሆኑን አቶ በየነ አያይዘው ገልፀዋል፡፡

የምስጢራዊ ህትመት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በየነ ጀምበሬ በቀጣይ ተመሳሳይ የሆኑ የሚስጥራዊ ህትመት ሥራዎችን ለማተምና የሚስጥራዊ ህትመት ሥራን  (ስፔሻላይዝ) ከማድረግ አንፃር የታቀዱና ወደተግባር የተገባባቸው ሥራዎች መኖራቸውን ገልፀው የቼክ ፐርሰናላይዜሽን ሥራ እንደ ምሳሌ አንስተው በውጭ ሀገር እየታተሙ የነበሩ የህትመት ዓይነቶችን በሀገር ውስጥ ለማተምና እየወጣ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡