ድርጅታችን ከአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከጥር 23 እስከ ጥር 27 2008 ዓ.ም ለአምስት ቀናት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን መከላከልና መቆጣጠር በተመለከተ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ የድርጅቱ የስልጠና ክፍል ኃላፊ አቶ ብርሀኑ አባይ እንደገለጹት ድርጅቱ ኢንዱስትሪ እንደመሆኑ መጠን እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት እንዴት መከላከል እና በሚደርሱበትም ወቅት በፍጥነት መቆጣጠር እንደሚቻል በጽንሰሃሳብና በተግባር የተመረኮዘ ስልጠና ለሰራተኞች መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኞች በሚሰለጥኑበት ወቅት የጽንሰሃሳቡን ስልጠና በማሰልጠኛ ክፍል ውስጥ ከወሰዱ በኋላ ያወቁትን በተግባር እንዲያሳዩ የተደረገበት ሲሆን በማንኛውም ጊዜና ወቅት አደጋዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ለዚሁ ተግባር ከተቋቋሙ መስሪያ ቤቶች ባለሙያዎች ወደ ድርጅቱ እስከሚመጡ አደጋውን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ስልጠናው በዋናነትም ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ ሲሆን ሰልጣኞች ግቢውን በማየትና ምልከታ በማድረግ አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ቀድመው ማምከን እንዲችሉ እና መከላከል እንዲቻል የሚያስችሉ ተግባራትን መፈጸም የሚያስችል ነው፡፡
ይህን መሰል ስልጠና በየዓመቱ የሚሰጥ ሲሆን በተለያየ ዙር ሠራተኞች ስልጠናውን እየወሰዱ በድርጅቱ ኮሚቴ ተዋቅሮ በቀጣይ ቋሚ በሆነ የግንኙነት ጊዜ በመምከር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ እና ከተከሰቱም ቀድሞ የመከላከል ስራውን እንዲሰሩ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡