የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በህትመት ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት በህትመት ኢንዱስትሪው ያለውን ችግር እንዲቀረፍ የበኩሉን ድርሻ ከመወጣት ባሻገር ለድርጅቱ በሚሊዬን የሚገመት ተጨማሪ ገቢ እያስገኘ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የህትመት ኮሌጁ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስፍን ካሳ እንደገለጹት፤ በየወቅቱ የሚሰጠው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ነው ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በእስከ አሁኑ አፈጻጸም 70 የድርጅቱ ሠራተኞች እና ከውጪ መጥቶ በማዕከሉ የተመዘኑ ከ30 በላይ ተመዛኞችን ጨምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ በተለያየ የሙያ ደረጃ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ተመዝነው ምዘናውን አልፈዋል ያሉት ዳይሬክተሩ የምዘናውም ዓላማ በአጠቃላይ በህትመት ዘርፍ ብሎም በዋናነት ደግሞ የድርጅቱ ምርትና አገልግሎት ወደ ተፈለገው የህትመት ስታንዳርድ እንዲሸጋገር ለማስቻል ይረዳል ብለዋል፡፡ እንደ ማናቸውም ሌሎች ድርጅቶች የህትመት ድርጅቱ የሚሰጣቸው የህትመት አገልግሎትና ምርት በስታንዳርድ የተለካ በማድረግ እና የተፈለገውን የጥራት ደረጃ ላይ ለማድረስ ኮሌጁ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል ያሉት አቶ መስፍን በተመዛኞችም መካከል የውድድር መንፈስ እንዲስፋፋ ከማድረጉም በላይ
ባለሙያዎች በሚሰሩት ሙያ በራስ የመተማመን ሁኔታን ያጎለብትላቸዋል ብለዋል፡፡
ኮሌጁ ከተቋቋመለት አላማ አንጻር በጥሩ ጅምር ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የተፈለገውን ግብ ለመምታት ግን በርትቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኮሌጁ ለድርጅቱ ተጨማሪ የገቢ ምንጭም እየሆነ ነው ያሉት አቶ መስፍን በያዝነው በጀት ዓመት በእስከዚህ ሩብ ዓመት በተለያየ መንገድ የተገኘ ከ1.3 ሚሊዬን ብር በላይ ገቢ አስገኝቷል ብለዋል፡፡ ኮሌጁ የተቋቋመው የድርጅቱን ሠራተኞች የክህሎት እና የሙያ ደረጃ ለማሳደግ ነው ያሉት አቶ መስፍን ሠራተኛው ዕድሉን በመጠቀም ራሱንና ድርጅቱን ሊጠቅም በሚችል ደረጃ በፍላጎትና በተነሳሽነት በሚሰጠው የስልጠና ድልድል መሰረት እውቀት መገብየት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በህትመት ኮሌጁ የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ የሆኑት አቶ ኩምሳ ካሮርሳ በበኩላቸው ኮሌጁ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ በየጊዜው የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው የብቃት ማረጋገጫ (COC) የሚሰጠው በሙያ ብቃት ማረጋገጫ ተቋማት በሚቀርበው ስታንዳርድ መሠረት ነው ብለዋል፡፡ የህትመት ኮሌጁ ከማተሚያ ድርጅት ሠራተኞች በተጨማሪ ከውጪ መጥቶ የሙያ ብቃት ለመፈትን ለሚፈልጉ ዜጎች የመመዘኛ ጣቢያ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል፡፡ ኮሌጁ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሆኖ እንዲያገለግል ምክንያት የሆነው መሰረታዊ የሙያ መመዘኛ አቅርቦቶችን (ማሽኖችን) እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ያሟላ ስለሆነም ነው ተብሏል፡፡ በህትመት ኮሌጁ በደረጃ (LEVEL) ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ያሉበትን ደረጃ ሲጨርሱ የብቃት ማረጋገጫ መመዘኛ ወስደው ሲያልፉ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ አልፎ እንዲማሩ ይደረጋል ያሉት አቶ ኩምሳ ሌሎች አጫጭር ስልጠናዎች ግን በሰልጣኞች ጥያቄ እና ፍላጎት መሰረት ሂደቱን በመከተል የብቃት መመዘኛ እንዲወስዱ ሁኔታዎች ይመቻችላቸዋል ብለዋል፡፡ አቶ ኩምሳ አያይዘው ኮሌጁ በዘርፉ ያለውን የክህሎት እና ዘመኑ የሚፈልገውን እውቀት በማስጨበጥ በህትመት ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት በመሙላት የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖር ብሎም በሀገራዊ ለውጥ ውስጥ ያለውን ፋይዳ እውን እንዲሆን ያስቸለዋልም ብለዋል፡፡
የህትመት ቴክኖሎጂ ዳይሬክተሩ አቶ መስፍን እንዳሉት፤ ኮሌጁ የበለጠ ውጤታማ ሆኖ ግቡን እንዲመታ የድርጅቱ የበላይ አመራር በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተግዳሮት ናቸው ያሏቸውን ችግሮች የጠቀሱት አቶ መስፍን ከተግዳሮቶቹም መካከል በሀገር ደረጃ በህትመት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትምህርት የሚሰጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባለመኖራቸው የኮሌጁ መምህራን የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡አያይዘውም ካለው የሰልጣኝ ብዛት እና ከውጪ ከሚመጣ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ጥያቄና ፍላጎት እንዲሁም ሌሎችንም ተጓዳኝ ሥራዎች በሚፈለገው ደረጃ ከመተግበር አንጻር የማሽን እጥረት አለ ያሉት ዳይሬክተሩ የችግሮቹም ምንጭ ከውጪ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የህትመት ኮሌጁ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ እና እንደ ሀገር በዘርፉ ያለውን ችግር በመቅረፍ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲደግፍ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አቶ መስፈን ጥሪ አቅርበዋል ፡፡