የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም አበረታች መሆኑ ተገለፀ፡፡

ድርጅቱ በግማሽ ዓመቱ 75,462,000 ብር አተረፈ፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተደዳር ኤጀንሲ የድርጅታችን የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም በኤጀንሲው መሰብሰቢያ አዳራሽ የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም ተገመገመ፡፡ የድርጅቱ የኦፕሬሽንና የለውጥ ስራዎች አፈፃፀም በአቶ መኮንን አበራ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር በኩል ቀርቧል፡፡ በቀረበው ሪፖርት ላይ የኤጀንሲው የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች አስተያየትና ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ሪፖርት በወቅቱ መላክ፣ የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ በተደራጁት ንኡሳን ኮሚቴዎችና በጋራ በመሆን በቅርበት ስራዎችን መከታተልና መደገፍ፣ የ2011 በጀት ዓመት የፋይናንስ አፈፃፀም በውጭ ኦዲተሮች በወቅቱ ኦዲት በማስደረግ እና ሪፖርቱ ንፁህ መሆኑን በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ለህብረተሰቡ ግልፅ መደረጉ እንዲሁም ከዚህ በፊት በኤጀንሲው የተሰጡትን አስተያየቶች በሚገባ ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ መደረጉ ጠንካራ ጎን መሆናቸውን እና ካሉት ግንባር ቀደም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አንዱ መሆኑን በኤጀንሲው የማኑፋክቸሪንግ ዳይሬክተር አቶ ገረመው ቀኖ ገልፀዋል ፡፡

በኤጀንሲው አመራሮችና ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ እንዲሁም የስራ አመራር ቦርድ እና ማኔጅመንት አባላት ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ በየነ ገ/መስቀል እንደተናገሩት የቦርድ አመራሮችና አባላት ድርጅቱን ለመደገፍ እያደረጉት ያለውን ጥረት፣ በድርጅቱ የኢንዳስትሪ ሰላም መስፈኑ፣ በሰራተኞች የሚነሱ ችግሮች ተቀራርቦ ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት፣ ሠራተኛው ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱና የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማሳካት እየተደረገ ያለውን ርብርብ እና ድርጅቱ ትርፋማ ሆኖ መቀጠሉ እንዲሁም የኮርፖሬት ገቨርናንስ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት መደረጉ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ይህን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የስራ አመራር ቦርዱ በህትመት ኢንዳስትሪውና ሌሎች የፋይናንስ ሪፖርቶች አረዳድ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ስልጠና መስጠት እንዲሁም በሪፎርም ላይ የተቀመጡ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በቀጣይ መሰራት እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡ ድርጅቱ አሁን ያለበት ደረጃ በጣም ጥሩ በሚባል የአፈፃፀም ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ክቡር አቶ በየነ ገልፀው በኤጀንሲው በኩል ድርጅቱን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ድርጅቱ በ6 ወራት ብር 135,793,788 የሚያወጣ ምርት ለማምረት አቅዶ አፈፃፀሙ ብር 133,053,058 የሚያወጣ ምርት ማምረት በመቻሉ አፈፃፀሙ 97.98% ሲሆን፣ ከተጣራ ሽያጭ ብር 261,141,900 ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ክንውኑ ብር 214,109,000 ሲሆን አፈፃፀሙ 82% ሆኗል፡፡ ከታክስ በፊት ብር 82,206,000 ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ  ክንውኑ ብር 75,462,000 ሲሆን አፈፃፀሙ  92% ሆኗል፡፡