ድርጅቱ መፃህፍት ለማሳተም አቅም ለሌላቸው ደራሲያን በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በኩል ድጋፎችን ማድረጉ የድርጅቱን ማህበራዊ ኃላፊነት በመወጣት አጋርነቱን እንደሚያሳይ ተገለፀ፡፡
የሰላሳ ስድስት አንጋፋና ወጣት ደራሲያን የስነ-ፅሑፍ ሥራዎችን ስብስብ የያዘ “ማህደረ ደራሲያን” መጽሐፍ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ፣ አንጋፋና ወጣት ደራሲያን በተገኙበት ህዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም የስጦታ ርክክብ ተደርጓል፡፡
“አንባቢዎች መሪዎች ይሆናሉ!” የሚል መሪ መልዕክት በተሰናዳው የሥጦታ መርሃ ግብር አንጋፋ ገጣሚና ፀሐፊ ተውኔት እና የማህደረ ደራሲያን መፅሐፍ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አያልነህ ሙላቱ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በመክፈቻ ንግግራቸው በደራሲያን የህይወት ተሞክሮ ዙሪያ ያተኮር መፅሐፍ እንዲፃፍና ታትሞ ለአንባቢያን እንዲደርስ ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ የነበሩ ሂደቶችን ለታዳሚው ገልፀው መፅሀፉን በአሳታሚነትና በአታሚነት ለንባብ ያበቃውን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ቀደም ባለው ዘመን ጀምሮ የማሣተም አቅም ለሌላቸው ደራሲያን በሚያደርገው የማተም ሥራ እንዲሁም ዘመናትን ለተሻገረው የድርጅቱና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ግንኙነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በመፅሐፍ ሥጦታ ሥነ ሥርዓቱ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትን ጨምሮ በማህደረ ደራሲያን መፃህፍት በደራሲነት እና በአርትኦት ሥራ የተሳተፉ ደራሲያንና እንዲሁም በተለያየ መልኩ እገዛ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት የምስጋና የምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መፅሐፍቱን ለማኅበሩ ያስረከቡት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በሀገራችን የህትመት ታሪክ ፈር ቀዳጅና አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ቀደም ሲል አዳዲስና አንጋፋ ደራሲያን እንዲበረታቱ ተዘዋዋሪ ፈንድ ሶስት መቶ ሺህ ብር በመመደብ በኢትዮጵያ ደራሲያን በኩል ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ መ
ሆኑን ገልፀው በተመሳሳይ ይህን “ማህደረ ደራሲያን” የተሰኘውን መፅሐፍ ደራሲያኑ አዘጋጅተው ለህትመት ወደ ድርጅቱ ባመጡት ጊዜ አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግላቸው ተገልፆ ለመታተም የሚያበቃውን ሂደቶች አልፎ ዛሬ ላይ ድርጅቱን ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ እና ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር መሰረት በማድረግ ግምቱ ሶስት መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ብር የሚሆነውን 7000 መፅሐፍ በስጦታ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አያይዘውም በድርጅቱ ተቋቁሞ የተለያዩ የምርት አጋዥ መፃህፍትና ሌሎች የድርሰት ሥራዎችን በማሣተም ሥራ የፐብሊሺንግ የሥራ ክፍል በአደረጃጀት ተካቶ ለተመሳሳይ ቀና እና ለጋራ ተጠቃሚነት መቋቋሙ እንደ ሀገርም የሚታየውን የዘርፉን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ በበኩላቸው ለማህበሩ ለተበረከተው የመፅሀፍ ሥጦታ ድርጅቱን አመስግነው በቀጣይ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በጋራ ሊሰሯቸው የሚችሉ ሥራዎች እንደሚኖሩ ገልፀዋል፡፡